ሰላም፤ ለአገራችን፣ ለቤታችን በተለይም ለልባችንና ለአእምሮአችን ሰላም የት ይገኛል? በሰዎች ዘንድ የሰላም የጥም ጩኸት ለዘመናት ሲያስተጋባ ኖርዋል፤ በተለይም ዓለም ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደ አውሎ ንፋስ እየተናወጠችና ለአስደንጋጭ ክስተቶች ተጋላጭ እየሆነች በመጣች ቁጥር የሰላም ጉጉት ጩኸት ጎልቶ ይሰማል፡፡ ያንተስ የልብህ ጥማት ይሄ ነው? አለመርካትና ሁከት በነገሰበት ዓለም ውስጥ ሁሉን የሚያስንቅ ውስጣዊ ፀጥታን ማግኘት ትፈልጋለህ?
ዓለምን ለኑሮ ተስማሚ እና የተሻለች ለማድረግ የታለመ መጨረሻ የሌለው የስልጣኔ ጉዞ ህይወትን የባሰ ውስብስብ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ምንም እንኳን ሰዎች በብዙ መልኩ ነገሮች ከወላጆቻቸው የተሻሉ ቢሆኑላቸውም እነርሱ ራሳቸው ግን የተሻሉ አይደሉም፡፡ ሰዎች በድካምና በስጋት ወስጥ ናቸው፡፡ ሰዎች ምሪት እና አማካሪ፣ ጥበቃ እና ዋስትና እንደሚያስፈልጋቸው አጠያያቂ አይደለም፡፡ ሁላችንም የአእምሮ ሠላም እንዲኖረን እንፈልጋለን፡፡
የአእምሮ ሰላም እንዴት ያለ ትልቅ ሀብት ነው! ይህን አይነት ሠላም ግጭትና ተስፋ መቁረጥ፣ አመፃና ችግር በበዛበት ዓለም ውስጥ ማግኘት ይቻል ይሆን?
ታላቁ ፍለጋ ቀጥሏል! ብዙዎች ዝናንና ገንዘብ በማካበት፣ በተድላና በስልጣን፣ በትምህርትና በእውቀት ብዛት እና ትዳር በመመስረት ሰላምን ለማግኘት ይሞክራሉ፡፡ አእምሮአቸውን በእውቀት መሙላት እና ሀብት ማካበትን ይፈልጋሉ፤ ነፍሳቸው ግን ባዶ እንደሆነች ትቀራለች፡፡ ሌሎች በአደንዛዥ እፅ እና በአልኮል የህይወትን ገሃድ (እውነታ) ከመጋፈጥ ለመሸሽ ይሞክራሉ ነገር ግን የሚፈልጉትን ሰላም አያገኙትም፡፡ ፍለጋቸው ሁሉ መውጫ ወደሌለው ተስፋ አስቆራጭና ከንቱነት እሽክርክሮሽ ውስጥ ያስገባቸዋል፡፡ በአስጨናቂው ዓለም ውስጥ ብዙዎች አሁንም በባዶነትና በብቸኝነት አእምሮአቸው እየተጨነቀ ይኖራሉ፡፡
ብዙዎች ውጫዊ ከሆነውና ከሚጨበጠው ነገር ሰላምን ለማግኘት ይጣጣራሉ፤ ወደ ውስጣቸው መመልከትን ግን ቸል ብለዋል፡፡ በውስጣቸው ሊገኝ የሚችለውን ይፈራሉና፡፡ ስለሚጨነቅ አእምሮአቸው አስጨናቂውን ዓለም ይኮንናሉ፡፡ ፈውስ ግን መጀመር ያለበት ከውስጥ ልባቸው ነው፡፡
ሰው በውጥረት ውስጥ
እግዚአብሔር ሰውን ከፈጠረው በኋላ በፍፁም ሰላም፣ ደስታ እና ተድላ መኖር እንዲችል ባማረ የአትክልት ስፍራ አስቀመጠው፡፡ ነገር ግን አዳምና ሄዋን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በተላለፉባት ሰአት ጸጸት ተሰማቸው ፡፡ በፊት የእግዚአብሔርን መገኘት ይናፍቁ ነበር፤ በኋላ ግን በሀፍረት እራሳቸውን ደበቁ፡፡ ያውቁት የነበረው ሰላምና ደስታ በጸጸትና እና በፍራቻ ተተካ፡፡ የዓለም ብሎም የአእምሮ ጭንቀት የጀመረው እዚህ ጋር ነበር፡፡
እንደ አዳምና ሄዋን አንተም ከእግዚአብሔር ሀሳብ ውጪ ስትሆን ህይወትህ በፍራቻና በጭንቀት ይሞላል፡፡ በኑሮህ እርግጠኛ ስላልሆንክባቸው ነገሮች፣ እየተለዋወጠ እና እያከተመለት ባለው ዓለም ላይ አስኩሮትህን ስታደርግ ሀሳብህን የጣልክበት እና የዋስትናህ መሰረት ይናጋል፡፡ ሰላም አይኖርህም ትረበሻለህ፡፡
ኃጢአት ሰውን ከእግዚአብሔር ለይቶታል፡፡”እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን” (ኢሳያስ 53፡6)፡፡ ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል (ሮሜ 3፡23)፡፡ ኃጢአት፣ ፍራቻ፣ ንዴት ራስ ወዳድነት እና ሌሎችም ጫና እያሳደሩበት ጠላት ሆነው ሰውን በሄደበት ሁሉ የሚከተሉት ቀንበር ሆነውበታል፡፡ እነዚህ መሰላቸትንና የአእምሮ ድካምን ያስከትላሉ፡፡
ራስ ወዳድነት ለሰው የመጀመሪያ አለመታዘዝ ስር መሰረት የጣለ ነበር፡፡ አሁንም ሰውን ወደ ተስፋ መቁረጥና ወደ ልብ ስብራት የሚገፋፋ መሰረታዊ ከሆኑ ክፉ ነገሮች አንዱ ነው፡፡ ለፍላጎቶችህና ለምኞቶችህ ራስወዳድ ከሆንክ ስግብግብ እና ጭንቀታም ያደርግሀል፡፡ በራስ ወዳድነትህ ብዙ ከቀጠልክ ጭንቀትህም እየጨመረ ይመጣል፡፡
እግዚአብሔርን ያማከለ ህይወት ሰላምን ይሰጣል
ራስህን የህልውናህ ማዕከል አድርገህ ከመመልከት ይልቅ ወደ እግዚአብሔር መለስ ብለህ እርሱን የህይወትህ አላማ ልታደርገው ያስፈልግሀል፡፡ እግዚአብሔር የህይወትህ ገዢ ካልሆነ ለጠባብ አስተሳሰብ፣ በራስ ለማዘን፣ ለፍራቻ እና ለጭንቀት በቀላሉ ተጋላጭ ትሆናለህ፡፡ መሪህ እግዚአብሔር ከሆነ ሕይወትህ በሁሉም አቅጣጫ የተሟላና በኑሮህም ደስተኛ ትሆናለህ፡፡ በእግዚአብሔር የምትመራ ልብ ብቻ በመረጋጋትና በሰላም ትኖራለች፡፡
መዝሙረኛው ዳዊት “ልቤ ጨካኝ ነው፥ አቤቱ፥ ልቤ ጨካኝ ነው፤ እቀኛለሁ፥ እዘምራለሁ” (መዝ. 57፡7) ብሎ ይናገራል፡፡ በሙሉ ልቡ እግዚአብሔርን በመታመኑ በአእምሮ እረፍት ሀሴት ማድረግ ችሏል፡፡ ልባችን በእግዚአብሔር ላይ ከተደገፈ በዙሪያችን አስጨናቂ ነገሮች ቢኖሩም ውስጣችን ግን ሰላም ይሆናል፡፡ “በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም” (2ቆሮ. 4፡8) እንደሚለው መሆን ይቻላል፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ የሰላም ምንጭ
ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ አላማ ወዳለው እና ማንነትን ወደ ሚለውጥ ህይወት ይጋብዛል፡፡ “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” (ማቴ. 16፡24)፡፡ “ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል” (2ቆሮ. 5፡17)፡፡ “ወደ እኔ ኑ” የሚለውን የኢየሱስን ጥሪ ትቀበላለህ? በጨለማ ምትክ ብርሀንን፣ በግራመጋባት ፈንታ መታመንን፣ ለታወከ ሰላምን፣ ላዘነ ደስታን፣ ለደከመ እረፍትን፣ተስፋ ለቆረጠ ተስፋን እና ለሞተው ህይወትን መስጠት ይችላል፡፡
እግዚአብሔር ሰውን ከአምላኳ ጋር መገናኘትን የምትጠማ ሕያው ነፍስ እንዲኖረው አድርጎ ፈጥሮታል፡፡ “ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደሚናፍቅ፥ አቤቱ፥ እንዲሁ ነፍሴ ወደ አንተ ትናፍቃለች። ነፍሴ ወደ ሕያው አምላክ ተጠማች፤ መቼ እደርሳለሁ? የአምላክንስ ፊት መቼ አያለሁ?” (መዝ. 42፡1-2)፡፡ ነፍስን ማርካት የሚችል ሕያው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ይሄን እርግጠኛ መሆን ትችላለህ፤ ከእግዚአብሔር ጋር ካልተስማማህ በቀር መቼም እውነተኛ ሰላም ሊኖርህ አይችልም፡፡
በልባችን ያለው የውጊያ ሜዳ
ነፍሳችን አምላኳን ብትጠማም በሀጢአት የተሞላ ማንነታችን ግን በእግዚአብሔር ላይ ያምፃል፡፡ ከፊል ማንነታችን እግዚአብሔርን ይናፍቃል ከፊሉ ደግሞ ወደ ስጋ ምኞት ይሳባል፡፡ ልባችን የማያቋርጥ ትግል ያለበት የውጊያ ሜዳ ነው፡፡ ይህ ውስጣዊ ትግል ለውጥረትና ጭንቀት ምክኒያት ይሆናል፡፡ ያለ እግዚአብሔር “እንደሚንቀሳቀስ ባሕር ናቸው፤ ጸጥ ይል ዘንድ አይችልምና፥ ውኆቹም ጭቃና ጕድፍ ያወጣሉና ” (ኢሳ. 57፡20) እንደሚለው ነን፡፡
ህይወታችን ማለትም አእምሮአችን፣ አካላችን እና መንፈሳችን በፈጠረንና እና በሚያውቀን በአንዱ በእግዚአብሔር ካልተስተካከለ በስተቀር ዘላቂ ሰላም ሊኖረን አይችልም፡፡ እርሱ የአለማት ጌታ ብቻ ሳይሆን የእኔን እና ያንተን ሕይወት ከጅማሬው እስከ ፍፃሜውም የሚያውቅ ነው፡፡ ስለኛ በማሰብ ወደ አለም መጣ “ብርሃኑም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት ያበራል እግሮቻችንንም በሰላም መንገድ ያቀናል” (ሉቃስ 1፡79)፡፡
የሰላም አለቃ የሆነ ኢየሱስ ወደ እሱ እንድትመጣ ይጠይቅሀል “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ ” (ማቴ. 11፡28)፡፡ ወደ እሱ ስትመጣ በሚሰጥህ ነፃነት እረፍትና እፎይታን ታገኛለህ፡፡ ሰላምህ እንደሚፈስ ወንዝ ይሆናል፤ “ሰላምህ እንደ ወንዝ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር፤ ” (ኢሳ. 48፡18)፡፡ ሸክምህን ሁሉ በእርሱ ላይ በማራገፍ ወደ ኢየሱስ ትመጣለህ? “ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ . . . ልባችሁ አይታወክ አይፍራም” (ዮሐ. 14፡27) ይልሀል፡፡
የፍርሀትና የስጋት መድሀኒት እምነት ነው፡፡ ከዘለአለም እስከ ዘለአለም የሚኖር፣ ከቶ የማይለወጥ ወዳጅ፣ ፍቅሩም የማያረጀውን እግዚአብሔርን መታመን እንዴት እረፍት ነው፡፡ ይህ ወዳጅ ሁሌም ያስብልናል፤ ይጠነቀቅልናል፡፡ ስለዚህ ለምን ሀሳብ ይግባን ለምንስ እንጨነቅ? በ 1ኛ ጴጥ. 5፡7 ላይ “እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት” የሚለውን መተግበርን ተለማመድ፡፡ ውጊያው ሲጠናቀቅ ሰላም አለ፤ ታዲያ ህይወትህን ለዚህ ጌታ ለምን አትሰጥም? አስታውስ፣ ካመንክ አትጨነቅም፤ ከተጨነክ አታምንም፡፡ “በአንተ ታምናለችና በአንተ ለምትደገፍ ነፍስ ፈጽመህ በሰላም ትጠብቃታለህ ” (ኢሳ. 26፡3)
ቅሬታ ወይም ንዴት የአእምሮህን ሰላም የሚሰርቅ መርዝ ነው፡፡ ወደ ተስፋ መቁረጥና ተስፋን ወደሚያጨልም ግራ መጋባት ይመራል፡፡ የበደሉህን ሰዎች ይቅርታ ለማድረግ ከባድ ሊሆን ይችላል፤ አንተ ይቅር መባል ከፈለክ ግን ይቅረታ ማድረግ ግዴታህ ነው፡፡ “ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ፥ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም” (ማቴ. 6፡15)፡፡ እምነት በልብህ ሲወለድ ፈቃድህን ለአምላክህ ማስገዛት አይከብድህም፡፡ ቂም ከመያዝና ከመበሳጨት ይልቅ ልብህ በፍቅርና በይቅርታ ይሞላል ከዚያ ውስጣዊ እርጋታን ታገኛለህ፡፡ ኢየሱስ የልብህ ገዢ ሲሆን ጠላቶችህን መውደድ ትችላለህ፡፡ የክርስቶስ ደም ነፃ ሲያወጣህ ብቻ ይህን ማድረግ ትችላለህ፡፡
ሀጢአትን መናዘዝ እና ንሰሀ መግባት የአእምሮ ሠላም ይሰጣል
ከዚህ በፊት የሰራሀቸው የሀጢአቶችህ ሸክም ከብዶህ መሸከም ከምትችለው በላይ እንደሆነ ተሰምቶህ ይሆናል፡፡ ጌታ ለከበደብህ ሸክም በ የሐዋ. ሥራ 3፡19 መፍትሄን ይሰጥሀል፡፡ “እንግዲህ ኃጢአታችሁ እንዲደመሰስ ንስሐ ግቡ፤ ከመንገዳችሁም ተመለሱ፤ በጌታም ዘንድ የመታደስ ዘመን ይመጣላችኋል(አ.መ.ት)”፡፡ (1ዮሐ. 1፡9) “በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው” ይላል፡፡ “እንግዲህ በእምነት ከጸደቅን በእግዚአብሔር ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እንያዝ” (ሮሜ 5፡1)፡፡
በመዝሙር 23 ላይ ዳዊት በእግዚያብሔር ላይ ያለውን እምነት ይገልፃል፡፡ በህይወቱ ስለተለማመደው ሰላም ሰፊ ማብራሪያ ይሰጣል፡፡ ሰላምና ህብረት ከእረኛው ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ላላቸው ሁሉ ነው፡፡
መዝሙር ሀያ ሶስት
እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፥ የሚያሳጣኝም የለም። በለመለመ መስክ ያሳድረኛል፤ በዕረፍት ውኃ ዘንድ ይመራኛል። ነፍሴን መለሳት፥ ስለ ስሙም በጽድቅ መንገድ መራኝ። በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኵዝህ እነርሱ ያጸናኑኛል። በፊቴ ገበታን አዘጋጀህልኝ በጠላቶቼ ፊት ለፊት ራሴን በዘይት ቀባህ፥ ጽዋዬም የተረፈ ነው። ቸርነትህና ምሕረትህ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ ይከተሉኛል፥ በእግዚአሔርም ቤት ለዘላለም እኖራለሁ።
ይሄን እረኛ ታውቀዋለህ? በእርሱ አምነሀል፣ ተደግፈሀል? ኢሳያስ ይህ ሩሩህ እና መሀሪ እረኛ “መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፥ ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል” (ኢሳ. 40፡11) ይለናል፡፡ ከግራ መጋባት ለመውጣትና ዘላለማዊ እረፍረት ወዳለበት የእግዚአብሔር ክንድ ውስጥ ለመግባት ዝግጁ ነህ፡፡ ይለፈውን የሀጢአተኝነት ህይወትህን፣ እያለፍክበት ያለውን ፈተናህን፣ የወደፊት ስጋትህን እና ሙሉ ማንነትህን ለጌታ አሳልፈህ ልትሰጠው ተዘጋጅተሀል፡፡ ጌታ ምርጫውን ያቀርብልሀል፡፡ መወሰን የአንተ ድርሻ ነው፡፡
ዘላቂ ሠላም
በሙሉ ልብህ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ስትመጣ የአእምሮ ሠላምን ለማግኘት የምታደርገው ፍለጋህ ያበቃል፡፡ እርሱን በማመን ብቻ የሚገኝን ሰላምና እረፍት ይሰጥሀል፡፡ እንደ ገጣሚው ለማለትም ትችላለህ፣
ሠላም በሌነበት፣ ሠላምን አውቃለሁ
ወጀብ ባንሰራራበት እርጋታ ያለበት
ሚስጥራዊ በሆነ ቦታ፣ ፊት ለፊት
ከጌታዬ ጋር ልሆን የምችልበት
ራልፍ ስፓልዲንግ ኩሽማን-
በአስጨናቂው ዓለም ሠላም ይኖርሀል! የልብህን በር ለክርስቶስ አሁን ክፈትለት፤ እርሱም አንድ ቀን ለዘላለም ፍፁም ዕረፍት ያለበት የመንግስተ ሰማይን በር ይከፍትልሀል፡፡