የሰው ልጅ ቅዱስ በሆነው በእግዚአብሔር ፊት በኃጢአቱ ወንጀለኛ ሆኖ በመገኘቱ ሞት እንደተፈረደበት ታውቃለህ? ከዚህ የዘላለም ሞት ፍርድ አምልጦ ለዘላለም ይድን ዘንድ የእግዚአብሔርን ምህረት መቀበል አለበት፡፡ ከዘላለም ሞት አንፃር ምህረት ማለት እግዚአብሔር የሰው ልጅ ሊቀበል ለሚገባው ፍርድ ይቅርታን ሲያደርግ ነው፡፡ ምንም እንኳ ድነት ነጻ የማይከፈልበትና በስራችን የምናገኘው ባይሆንም እግዚአብሔር ግን ምህረቱን ለሰው ልጅ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አይደለም የሰጠው፡፡ እግዚአብሔር ምህረት የሚደርግበት ቅድመ ሁኔታ ንስሐ ነው፡፡
መጥምቁ ዮሐንስ የእግዚአብሔርን ቃል እየሰበከ ሲመጣ ግልጽና ጠንካራ የነበረው መልዕክቱ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” (ማቴዎስ 3፥20) የሚል ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስም አገልግሎቱን የጀመረው “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” (ማቴዎስ 4፥17) በሚል ተመሳሳይ መልዕክት ነበር፡፡ ሐዋርያው ጴጥሮስ በ(የሐዋርያት ስራ 3፥19) ላይ “ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ ተመለሱም” እንዳለው ለመዳን ንስሐ መግባት አስፈላጊ ነው፡፡ የምህረት በር ተከፍቶ ድነት የሚገኘው በንስሐ አማካኝነት ነው፡፡
ሁሉ ኃጢአትን ሰርተዋል
በዓለማችን ቁጥሩ እጅግ የበዛ ሕዝብ ሲኖር፤ በብዙ መንገዶች አንዳችን ከአንዳችን እንለያያለን፡፡ ነገር ግን “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል” (ሮሜ 3፥23) የሚለውን መልዕክት ሁላችንም እንጋራዋለን፡፡ ጨምሮም “ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ” (ሮሜ 3፥10) ይላል፡፡ እግዚአብሔር በነብዩ ኢሳይያስ ሲናገር “እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ” (ኢሳይያስ 53፥6) ይላል፡፡ የነዚህን ጥቅሶች ዋና ሐሳብ ልብ ብለሀል? “እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ”፤ “አንድም ጻድቅ የለም”፤ ““ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋል”፡፡ እነዚህ ጥቅሶች አንተን አያካትቱ ይሆን? ነብስህና ሕይወትህ የእግዚአብሔር ነው፡፡ ወንድም ይሁን ሴት ማንም እግዚአብሔርን የሕይወቱ ጌታ አድርጎ የማይቀበል ሁሉ በአመጻና በኃጢአት ይኖራል፡፡ “ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች” (ሕዝቅኤል 18፥4)፡፡
ኃጢአት ያለያያል
ኃጢአትህ ከእግዚአብሔር ጋር አለያይቶሀል፡፡ ልትገልጸው የማትችለው ናፍቆት በውስጥህ ይሰማሀል፡፡ የተረሳህና እግዚአብሔርም የማይሰማ ሊመስልህ ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ይህ ለምን እንደሆነ ምክንያቱን እንዲህ ሲል ይነግረናል፡- “እነሆ፥ የእግዚአብሔር እጅ ከማዳን አላጠረችም፥ ጆሮውም ከመስማት አልደነቈረችም ነገር ግን በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል ለይታለች፥ እንዳይሰማም ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል (ኢሳይያስ 59፥1-2)። ጨምሮም (ሮሜ 6፥23) ላይ “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው” ይለናል። ስለ ሕይወትህና ስለ ኃጢአትህ ስታስብ ስለ እግዚአብሔርም አስብ፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ኃጢአት የለም፡፡ ስለዚህ እርሱ ቅዱስ ጻድቅና የማያዳላ አምላክ ነው፡፡ “እግዚአብሔር ሥራን ሁሉ የተሰወረውንም ነገር ሁሉ፥ መልካምም ቢሆን ክፉም ቢሆን፥ ወደ ፍርድ (በማምጣት)” (መክብብ 12፥14) ለኃጢአት ፍርድ እንደሚገባው ይነግረናል። በአንተና በእግዚአብሔር መካከል ሰፊ መራራቅ ተፈጥሯል፡፡ በቅዱሱ እግዚአብሔር እና በኃጢአተኛው ሰው መካከል የተፈጠረውን መራራቅ የሚያስታርቀውን መንገድ እስካላገኘህ ድረስ የዘላለም ሞትን ትሞታለህ! (ሉቃስ 16፥26)፡፡ ነገር ግን የምስራች፣ መንገድ አለ፣ ተስፋም አለልህ!
እግዚአብሔር በኃጢአት ላይ የሞትን ፍርድ ያስተላለፈ ቢሆንም፤ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” (1ዮሐንስ 4፥16) እንደሚል እርሱ የፍቅር አምላክ ነው፡፡ በኃጢአት የምትኖር እንኳን ቢሆን እግዚአብሔር ይወድሀል፡፡ ከፍቅሩ የተነሳ ትድን ዘንድ መንገድን አዘጋጅቶልሀል (ዮሐንስ 3፥16)፡፡ እግዚአብሔር በኃጢአት ላይ የፈረደውን ፍርድ ቢፈጽም ሰው በቅጽበት ይሞታል፡፡ ነገር ግን ማንም እንዲይጠፋ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የኃጢአታችንን ቅጣት ተቀብሎልን በሕይወት እንኖር ዘንድ ልጁን ኢየሱስን ልኮልናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ጭከና ተመልከት” (ሮሜ 11፥22) ይላል፡፡ የእግዚአንሔር ቸርነት ሰው ሁሉ እንዲድን መፈለጉ ሲሆን ፍርዱ ደግሞ መቀጣት ያለበትን ሁሉ ይቀጣል፡፡
ኢየሱስ ወደዚህ ዓለም የመጣው ነብሳችንን ለማዳን ነው፡፡ እርሱ ምንም ኃጢአት ያልተገኘበት ቅዱስ የእግዚአብሔር በግ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ለኛ ያለው ፍቅር የተረጋገጠው ኃጢአትና በደላችንን ሁሉ ወስዶ በኢየሱስ ላይ ባኖረበት ግዜ ነው፡፡ ቸርነቱን ተመልከት! ኢየሱስ በኛ ቦታ ሆኖ ኃጢአት በመሆን የእግዚአብሔር ፍርድ እንዲፈጸም በመስቀል ላይ ተሰቀለ፡፡ መከራና ስቃይንም ተቀብሎ ሞተ፡፡ የኃጢአታችንም ዋጋ ተከፈለ፡፡ የእግዚአብሔርን ጭካኔ ተመልከት!
ንስሐ፣ የእኛ ድርሻ
ኢየሱስ እንደሞተልህ ትረዳ ይሆን? በኃጢትህ ምክንያት መሞቱንስ ታስተውል ይሆን? ኢየሱስን የሰቀለው ማን ነበር? የአይሁድ መሪዎች፣ ጲላጦስ ወይስ የሮም ወታደሮች ብቻ ይሆኑ ለኢየሱስ መሰቀል ተጠያቂዎች? ሐዋርያው ጴጥሮስ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሲሰብክ “……ሰቅላችሁ ገደላችሁት” በማለት ይሰሙት የነበሩት ህዝብ ለኢየሱስ መሰቀል ተጠያቂዎች እንደነበሩ በ(የሐዋርያት ስራ 2፥16) ላይ ሲነግራቸው እናነባለን፡፡ ተሰቅሎ ወደነበረው ኢየሱስ ተመልከትና ለኃጢአተኛነትህ እውቅናን ስጥ፡፡
የጠፋህ መሆንህና እርዳታ እንደሚያስፈልግህ በእግዚአብሔር መንፈስ ኃይል ትረዳለህ፡፡ ይህ መረዳት በልብህ እየጠነከረ ሲመጣ የኃጢአተኝነት ሸክም በርትቶ ስለ ኃጢአትህ መጸጸት እንዲሆንልህ ያደርጋል፡፡ ያን ጊዜም “እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ” (ሉቃስ 18፥13) በማለት ወደ እግዚአብሔር መጮህ ይሆንልሀል፡፡ እግዚአብሔርም ከልብ የሆነ ጩኸትህን ሰምቶ ያድንሀል፡፡ ሸክምህም ሁሉ ተራግፎልህ ዳግም ትወለዳለህ፡፡ ኢየሱስን መከተልህን ስትቀጥል ከኃጢአት መንገዶችህ ሁሉ ፊትህን በማዞር ሰማያዊውን መንገድ ትከተላለህ፡፡ እግዚአብሔር ወደ እርሱ ለሚመጡ ሁሉ በልባቸው የሚሰራው ስራ እና የንስሐ መንገድ ይህን ይመስላል፡፡ ልብህ ታጥቦና ነጽቶ ሰላም ደስታና መተማመን ይሆንልሀል፡፡
በመጨረሻም ንስሐ በክርስቶስንና በእግዚአብሔርን ፍቃድ ደስ እየተሰኘህ አመስጋኝና ታማኝ እንድትሆን ያደርግሀል፡፡ ሞት ተፈርዶብንና መውጫው ጠፍቶን ሳለ ክርስቶስ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ” (ማቴዎስ 11፥28) አለን። “እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን” (1ዮሐንስ 4፥19)፡፡