ክፍሊቱ
መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ሙታንንም ታናናሾችንና ታላላቆችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፥ መጻሕፍትም ተከፈቱ፤ ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው፤ ሙታንም በመጻሕፍት ተጽፎ እንደ ነበረ እንደ ሥራቸው መጠን ተከፈሉ” (ራእይ 20፥12) የሚል ጥቅስን እናነባለን፤ ይህም እግዚአብሔር የእያንዳንዳችንን ሕይወት መዝግቦ እንደሚያስቀምት ማስረጃ ነው፡፡
በአሜሪካን አገር ሜሪላንድ ከተማ ነዋሪ የሆነው ጆሽዋ ሄሪስ የተባለ አንድ ወጣት የተወሰነ ጊዜን ለማሳለፍ ፖርቶሪኮ የተባለች ሀገር ነበር፡፡ በዚች ሀገር በነበረው ቆይታም አንድ ምሽት ሕልምን አለመ፡፡ ይህ ወጣት እግዚአብሔር ይህን ህልም ያሳየው ታማኝነት ከጎደለው የሕይወት ጉዞው እንዲመለስ ሊገስጸው እንደሆን ተሰማው፡፡ በዛን ምሽት ያየው ሕልም ሕይወት መቀየር የሚችለውን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይል እና የደሙን ጉልበት አስታውሶታል፡፡ እኛም ይህ ወጣት ያየውን ሕልም ልናካፍልህ እንወዳለን፡፡
(ክፍሊቱ)
በእንቅልፍ ሰመመን ውስጥ ሆኜ እራሴን በአንዲት ክፍል ውስጥ አገኘሁት፡፡ በዚህች ክፍል ውስጥ አንደኛውን የክፍልዋን ግድግዳ ከሸፈነው ትንንሽ የስምና የአድራሻ ማውጫ አይነት ካርዶችን የያዙ ማህደሮች ከተደረደሩበት መደርደሪያ በስተቀር ምንም የተለየ ነገር አልነበረም፡፡ እነዚህ ማህደሮች በቤተ መጽሐፍት ውስጥ ደራሲን ወይም የመጽሐፍን ርዕስ ተጠቅመን መጽሐፍ እንደመናወጣባቸው ካርዶች በፊደል ቅደም ተከተል የተደረደሩ ነበር፡፡ እነዚህ ማህደሮች ከወለሉ አንስተው እስከ ጣራው ድረስ ተደርድረው በሁለቱም አቅጣጫ መጨረሻ የሌላቸው ይመስሉ የነበር ሲሆን ሁሉም ማህደሮች የተለያዩ ርዕሶችን ይዘው ነበር የተደረደሩት፡፡ ማህደሮቹ ወደ ተደረደሩበት ግድግዳ እየተጠጋሁ ስመጣ “የወደድኳቸው ልጃገረዶች” የሚል ርዕስ ያለው ማህደር ቀልቤን ሳበው፡፡ ይህን ርዕስ የያዘውን ማህደር በመግለጥ ካርዶቹ ላይ የተጻፉትን ማንበብ ጀመርኩ፡፡ በካርዶቹ ላይ ተጽፈው የነበሩትን ስሞች አውቃቸው ስለነበር ደንግጬ በፍጥነት ማህደሩን ዘጋሁት፡፡
ከዛም ማንም ምንም ሳይነግረኝ የት እንደምገን ተገነዘብኩ፡፡ ይህቺ ማህደሮች የታጨቁባት ሕይወት አልባ ክፍል የእኔም ሕይወት ተመዝግቦ የተቀመጠባት ‘ማህደር ክፍል’ እንደሆነች ተረዳሁ፡፡ በዚህች ክፍል ውስጥ ላስታውሳቸው ከምችላቸው በላይ ትልቁም ይሁን ትንሹ እያንዳንዱ የሕይወት ክንዋኔዎቼ ተመዝግበው ተቀምጠዋል፡፡
አለፍ አለፍ እያልኩ የተለያዩ ማህደሮችን እያነሳሁ በውስጣቸው ተጽፎ የሰፈረውን ማንበብ ስጀምር መገረምና ጉጉት ከፍርሀት ጋር ውስጤን ሲወረኝ ተሰማኝ፡፡ ከማነባቸው ነገሮች አንዳንዶቹ ደስታን እና ጣፋጭ ትዝታን ሲያጭሩብኝ ሌሎች ግን ወደ ኋላዬ በመዞር ከበስተጀርባዬ የሚያየኝ ሰው ያለ እስኪመስለኝ ድረስ ሀፍረት እና ጸጸትን ይጭሩብኝ ነበር፡፡ “ወዳጆች” የሚል ማህደር “የከዳኋቸው ወዳጆች” ከሚል ማህደር አጠገብ ተቀምጦ ነበር፡፡
ማህደሮቹ ካደረኳቸው ተራ ነገሮች አንስቶ እስከ ተገለጡ ትልልቅ ክፋቶቼ ድረስ በተለያየ ርዕስ ተመዝግበው ተቀምጠው ነበር፡፡ “ያነበብኳቸው መጽሐፍት”፣ “የተናገርኳቸው ውሸቶች”፣ “ለሌሎች ሰዎች ያደረኳቸው ማጽናናቶች”፣ “የሳቅሁባቸው ቀልዶች” የሚሉ ሁሉ ይገኙ ነበር፡፡ “ወንድሞቼ ላይ የጮህኳቸው ነገሮች” የሚል ርዕስ ያለው አይነት ማህደሮችን ስመለከት የርዕሶቹ ትክክለኛነት በራሱ ያስቀኝ ነበር፡፡ እንደ “ቤተሰቦቼ ላይ ያኩተመተምኳቸው ነገሮች” አይነት ርዕስ ያላቸው ማህደሮች ደግሞ ምንም የማያስቁ ነበሩ፡፡ የተለያዩ ካርዶችን ባነበብኩበት ጊዜ ሁሉ ካርዶቹ ላይ ተጽፈው በነበሩት ዝርዝር ይዘቶች መደነቄን አላቆምኩም ነበር፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ከጠበኳቸው በላይ ካርዶች በአንድ ማህደር ውስጥ የነበሩ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ተስፋ ካደረኳቸው ካርዶች ያነሱ ካርዶች ነበሩ፡፡
እነዚህን ማህደሮች ማየቴ ይህን ሁሉ ነገር አድርጊያለሁ ወይ ብዬ እንድገረም አድርጎኛል፡፡ በሀያ አመታት እድሜዬ እነዚህን በሺዎች ምናልባትም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ካርዶችን ለመጻፍ የሚያስችል በቂ ጊዜ ነበረኝን? እያንዳንዱ ያየሁት ካርድ ግን ጊዜ እንደነበረኝ የሚያስረግጥ ነበር፤ ምክንያቱም እያንዳንዱ ካርድ በራሴ የእጅ ጽሁፍ የተጻፈ እና የራሴው ፊርማ ያረፈበት ነበር፡፡
“የሰማኋቸው ዘፈኖች” የሚል ርዕስ ያለበትን ዶሴ አውጥቼ ስመለከት የዶሴው ይዘት እየጨመረ ሲሄድ ይታወቀኝ ነበር፡፡ ካርዶቹ በጣም ተጠጋግተውና ተጠቅጥቀው ተቀምጠው የነበረ ሲሆን ከሁለትና ሶስት ሜትር በኋላ እንኳን የማህደሩውን መጨረሻ ማግኘት አልቻልኩም ነበር፡፡ እነዚህን ሁሉ ሙዚቃዎች ለማዳመጥ ባባከንኩት ጊዜ አፍሬ ማህደሩን ዘጋሁት፡፡
“የዝሙት ምኞት” የሚል ርዕስ ያለው ማህደር ጋር ስደርስ ሰውነቴን ሲቀዘቅዘኝ ተሰማኝ፡፡ የማህደሩን ትልቀት ላለማየት በትንሹ ሳብ አደረኩትና አንድ ካርድ ከውስጡ አወጣሁ፡፡ በላዩ ላይ ሰፍሮ የነበረውን ዝርዝር ይዘት ሳነብ በፍርሀት ተንቀጠቀጥኩ፡፡ እንዲህ አይነት አሳፋሪ ጊዜ ተመዝግቦ በመቀመጡ ሕመም ተሰማኝ፡፡
ድንገት ኃይለኛ ቁጣ በውስጤ ሲቀሰቀስ ታወቀኝ፡፡ “እነዚህን ካርዶች ማንም ማየት የለበትም! ማጥፋት አለብኝ!” የሚለው ሀሳብ ተቆጣጠረኝ፡፡ እንደ እብድ አድርጎኝ ማህደሩን ጎትቼ አወጣሁት፡፡ ምንም ትልቅ ቢሆንም አስብ የነበረው በውስጡ ያሉትን ካርዶች አራግፎ ማቃጠል ነበር፡፡ ነገር ግን ካርዶቹን ከማህደሩ ውስጥ አውጥቼ ወለሉ ላይ ለማራገፍ ስሞክር አንድም ካርድ ማውጣት አልቻልኩም፡፡ ካርዶቹን በእጄ በመያዝ ለመቀዳደድ ብሞክርም እንደ ብረት ጠንካራ የሆኑ በመሆናቸው ማንም ላደርግ አልቻልኩም፡፡
ተሸንፌ እና ተስፋ ቆርጬ ማህደሩን ወደ ነበረበት ቦታ መለስኩት፡፡ ግንባሬን ግድግዳው ላይ አስደግፌ በራሴ በማዘን በረጅሙ ተነፈስኩ፡፡ ድንገት ወደ ማህደሮቹ ስመለከት “ወንጌልን የሰበኩላቸው ሰዎች” የሚል ርዕስ የያዘ ማህደር አየሁ፡፡ የዚህ ማህደር እጀታ በአጠገቡ ካሉ ማህደሮች ደመቅ ያለ ሲሆን ምንም ያለተነካ በመሆኑ አዲስ ነበር፡፡ ይህን ማህደር ይዤ ስስበው ርዝመትዋ ከስምንት ሴንቲ ሜትር ያልበለጠች ትንሽዬ ሳጥን እጄ ላይ ወደቀች፡፡ በውስጥዋ የነበረው ካርድ ብዛት በአንድ እጄ ልቆጥረው የምችለው ነበር፡፡
ከዛም እንባ በአይኔ ላይ ግጥም አለና ማልቀስ ጀመርኩ፡፡ በጉልበቴ ተንበርክኬ ከሆዴ ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ፡፡ አለቅስ የነበረው ከተሰማኝ ታላቅ የሀፍረት ስሜት የተነሳ ነበር፡፡ እንባ ያዘሉ አይኖቼ በማህደሮች የተሞላውን መደርደሪያ ተመለከቱት፡፡ ስለዚህ ክፍል ማንም ሰው በፍጹም ማወቅ የለበትም፤ ቆልፌ ቁልፉን መደበቅ አለብን ብዬ አሰብኩ፡፡
እንባዬን ከአይኔ እየጠራረኩ እያለ ድንገት አየሁት፡፡ ወይኔ፣ በፍጹም እሱ መሆን የለበትም፡፡ እዚህ ቦታ ካልጠፋ ሰው ኢየሱስ ይገኛል ብዬ ያየሁትን ማማን አቃተኝ፡፡
ማህደሮቹን እየከፈተ ካርዶቹን ሲያነብ በተስፋ መቁረጥ እመለከተው ነበር፡፡ ምን ይለኝ ይሆን የሚለውን ሳስብ ከአቅሜ በላይ ሆነብኝ፡፡ ቀና ብዬ ፊቱን አተኩሬ ለማየት አቅም አጣሁ፡፡ ነገር ግን ከኔ በላይ ሀዘን እንደተሰማው ያስታውቅ ነበር፡፡ ሆን ብሎ መጥፎ መጥፎ የተመዘገበባቸውን ማህደሮች እያወጣ የሚያነብ መሰለኝ፡፡ እያንዳንዱን ነገር የሚያነበው ለምንድን ነው?
በመጨረሻ ዞር ብሎ በሀዘን ስሜት ተመለከተኝ፡፡ አስተያየቱ ንዴትን ሳይሆን ራሴን ዝቅ አድርጌ፣ ፊቴን በእጄ ሸፍኜ ድጋሚ ማልቀስ እንድጀምር አደረገኝ፡፡ ወደ እኔ መጣና በእጆቹ ትከሻዬ ላይ አቀፈኝ፡፡ ብዙ ብዙ ነገሮችን ማለት ሲችል ምንም ሳይናገር አብሮኝ አለቀሰ፡፡
ከዛም ብድግ ብሎ ወደ ማህደሮቹ ሄደ፡፡ ከአንዱ ጥግ ጀምሮ ማህደሮቹን እየመዘዘና እያንዳንዱን ካርድ እያወጣ የእኔን ስም እየሰረዘ በስሙ መተካት ጀመረ፡፡
“በፍጹም አይሆንም!” ብዬ በመጮህ በፍጥነት ቆሞ ወደ ነበረበት ቦታ ሄድኩ፡፡ ይዞት የነበረውን ካርድ ተቀብዬው በወቅቱ ማለት የቻልኩትን “በፍጹም አይሆንም” የሚለውን ቃል ደጋግሜ አልኩት፡፡ ስሙ በእነዚህ ካርዶች ላይ በፍጹም መጻፍ የለበትም ብዬ አሰብኩ፡፡ ነገር ግን በደማቅና የሚያምር ቀይ ቀለም የእኔ ስም ጠፍቶ የእርሱ ስም ተተካ፡፡ በደሙ ነበር የተጻፈው፡፡
በእርጋታ ካርዱን ከተቀበለኝ በኋላ በሀዘን የተሞላ ፈገግታን ፈገግ ብሎ ካርዶቹ ላይ ስሜን በስሙ መተካትና መፈረሙን ቀጠለ፡፡ እንዴት እንደሆነ በፍጹም ልረዳው ባልቻልኩት ፍጥነት የመጨረሻውን ካርድ ፈርሞ ማህደሩን በቦታው አስቀምጦ አጠገቤ መጥቶ ሲቆም አየሁት፡፡ እጁን ትከሻዬ ላይ አድርጎ “ተፈጸመ” አለ፡፡
ተንስቼ ቆምኩና እየመራኝ ከክፍሊቱ ወጣን፡፡ በክፍሊቱ በር ላይ ምንም ቁልፍ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ገና የሚጻፍባቸው ብዙ ባዶ ካርዶች ነበሩ፡፡
*****
እግዚአብሔር ሕይወትህን እንዴት እንደሚመለከተው አስበህ ታውቅ ይሆን? “እኔ እላችኋለሁ፥ ሰዎች ስለሚናገሩት ስለ ከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል” (ማቴዎስ 12፥36)፡፡ ለራሳችን ታማኞች ብንሆንና ባንዋሽ ደጋግመን በሀሳባችን እና በድርጊቶቻችን ኃጢአት መስራታችንን በሀዘንና በጸጸት እናምናለን፡፡ እኛም በሚስጥር ስላሰላሰልናቸው ሀሳቦች እና ስለሰራናቸው ስራዎች ማፈራችን አይቀርም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በሮሜ 2፥16 ላይ “እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ……..በሰው ዘንድ የተሰወረውን በሚፈርድበት ቀን ይሆናል” ይላል፡፡ ሐዋርያው ጴጥሮስ “እንግዲህ ከጌታ ፊት የመጽናናት ዘመን እንድትመጣላችሁ……..ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ ተመለሱም” (የሐዋርያት ሥራ 3፥19) ብሎ ሰብኳል፡፡ ኃጢአትህ በኢየሱስ ተደምስሶለሀል ነው ወይንስ ዛሬም ያሳድድሀል?
ነጻ መውጣት ትፈልጋለህን? ያለፈው ሕይወት ዘመንህ የሀሳብ እና የድርጊት ኃጢአት ሸክም ከብዶብሀልን? ኃጢአቶቻችን የልባችን እና የሕይወታችን ከባድ ሸክም ናቸው፡፡ “ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም” (1ኛ ዮሐንስ 1፥8)፡፡ “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው” (ሮሜ 6፥23)።
ኢየሱስ ዛሬም ምህረትን ያደርጋል፡፡ ወደ አለም የመጣውና ደሙን ያፈሰሰው ለኃጢአተኞች ሁሉ ነው፡፡ እግዚአብሔር አቅዶት የነበረው የመዳን መንገድ ተገልጥዋል፡፡ መዳን ትወዳለህን? “እንግዲህ ልጁ አርነት ቢያወጣችሁ በእውነት አርነት ትወጣላችሁ” (ዮሐንስ 8፥36) ፤ (መዝሙር 51)። ወደ ኢየሱስ አሁን ና! ተጸጽተህ ኃጢአትህን ሁሉ ተናዘዝ፡፡ “በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው” (1ኛ ዮሐንስ 1፥9)። ኢየሱስ ከእርሱ ጋር እርካታ ወደ ሞላበት ሕይወት እንደሚመራህ እመነው፡፡ በእለት ተእለት የሕይወት እርምጃህ ምሪትን ይሰጥሀል፡፡
ክፍሊቱ - የባለቤትነት መብት 1995
New Attitudes/ Joshua Harris.