ሁሉም ሰው ይህንን “እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል?” የሚለውን ጠቃሚ ጥያቄ እራሱን ሊጠይቅ ይገባዋል፡፡ ብዙ ሰዎች ድነናል ብለው ቢያምኑም ኢየሱስ ግን ሲናገር “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም” (ማቴዎስ 7፥21) ብልዋል፡፡ ድነትን ለማግኘት ክርስቶስ ኃጢአታችንን ይቅር እንደሚለን ማመን አስፈላጊ ነው፡፡ ከዛም ኃጢአታችንን መናዘዝ፣ በቅድስና መኖርና አንዳችን አንዳችንን በመውደድ በፍቅር ልንኖር ይገባል፡፡ በዚህ ዘመን የተለያዩ ኃይማኖቶች የተለያዩ ትምህርቶችን የሚያስተምሩ ሲሆን ሊጠየቅ የሚገባው መሰረታዊ ጥያቄ ግን “እውነት የትኛው ነው?” የሚለው ጥያቄ ነው፡፡
“ዳግም መወለድ” ማለት ምን ማለት ነው?
ብዙ ሰዎች ዳግም የመወለድ ልምምድን በሕይወታቸው ሳይለማመዱ ጌታን ሊያገለግሉ ሲሞክሩ ይታያሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች በርግጥ ድነዋልን? ኢየሱስ “ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” (ዮሐንስ 3፥3) ብልዋል፡፡ ኢየሱስ ይህቺን አለም ለቆ ሲሄድ መንፈስ ቅዱስን ልኳል፡፡ “እርሱም (መንፈስ ቅዱስ) መጥቶ ስለ ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ይወቅሳል” (ዮሐንስ 16፥8)፡፡ ሰውን ኃጢአተኛ እንደሆነ ወደ መረዳት የሚያመጣው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ሰው የኃጢአተኝነቱ ሸክም እየከበደበት ሲመጣ በልቡ የኃጢአተኛነት ወቀሳ እየተሰማው ይመጣል፡፡ ያ ሰው እራሱን ዝቅ ካደረገና ወደ እግዚአብሔር በእምነት በኢየሱስ በኩል ከጮኸ እግዚአብሔር ይቅር ይለዋል፡፡ “ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ ተመለሱም” (የሐዋርያት ሥራ 3፥19)፡፡ ከኃጢአት ንስሀ መግባት ማለት ለሰሩት ኃጢአት መጸጸት፣ የኃጢአት ልምምድን መተውና በአዲስ ሕይወት መመላለስን ያጠቃልላል፡፡ ይህ ሲሆን መንፈስ ቅዱስ በልባችን አድሮ ዳግም የተወለድን አዲስ ፍጥረት እንሆናለን፡፡ “ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል” (2ኛ ቆሮንቶስ 5፥19)፡፡
ዳግም መወለድ የሚያስፈልገው ለማን ነው?
“ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል” (ሮሜ 3፥23)፡፡ ነብዩ ኢሳይያስ በመንፈስ ቅዱስ በመነዳት “እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ” (ኢሳይያስ 53፥6) በማለት ጌታችን ኢየሱስ ስለ ሰው ልጆች ሁሉ ሊቀበል ስላለው መከራ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር፡፡ ኢየሱስ እውነትን ለማወቅ ፈልጎ ለመጣው ኒቆዲሞስ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አንደማይችል በግልጽ ነግሮታል፡፡ መንፈሳዊ መወለድ የመንፈስ ቅዱስ ስራ ነው፡፡ መዳን የሚፈልጉ ሁሉ ይህንን መወለድ ሊለማመዱ ይገባል፡፡
በኃጢአታቸው ሸክም የደከሙና የዛሉ ሁሉ ወደ ኢየሱስ በመምጣት ለኃጢአታቸው ምህረትን እንዲቀበሉ ተጋብዘዋል፡፡ ኢየሱስ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ፡፡ ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና” (ማቴዎስ 11፥28-30) በማለት ዛሬም ግብዣውን ያቀርባል፡፡ ኢየሱስ መከራን ተቀብሎ፣ ደሙን አፍስሶ “ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት” (1ኛ ዮሐንስ 2፥2) በመስቀል ላይ ሞትዋል፡፡
ንስሐ
ንስሐ መግባት፣ ኃጢአታችንን መናዘዝና መመለስ ወደ ጌታ ኢየሱስ በፍጹም ልባችን፣ ነብሳችን፣ ሀሳባችንና ኃይላችን የምንመጣባቸው ሂደቶች ናቸው፡፡ “ኃጢአቱን የሚሰውር አይለማም የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል” (ምሳሌ 28፥13)። “በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው” (1ኛ ዮሐንስ 1፥9)። የበደልነውና ያስቀየምነው ሰው ካለ ኃጢአታችንን ተናዘን፣ የበደልነውና ያስቀየምነውን ሰው ይቅርታ ጠይቀን መክፈል ወይም መመለስ ያለብንን ሁሉ ከፍለንና መልሰን ሰላምን ልናወርድ ይገባናል፤ “ዘኬዎስ ግን ቆሞ ጌታን። ጌታ ሆይ፥ ካለኝ ሁሉ እኵሌታውን ለድሆች እሰጣለሁ፤ ማንንም በሐሰት ከስሼ እንደ ሆንሁ አራት እጥፍ እመልሳለሁ አለው” (ሉቃስ 19፥8)።
እምነትና መታዘዝ
ዳግመኛ መወለድን ከተለማመድን በኋላ በታማኝነት የተሞላ የክርስትና ሕይወትን ለመኖር መትጋት አለብን፡፡ ኢየሱስ ለተከታዮቹ “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” (ማቴዎስ 16፥24) በማለት ተዕዛዝ ሰጥትዋል። በዓለም ከሚገኝ እድፍም እራሳችንን እንድንጠብቅ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶናል (ያዕቆብ 1፥27)፡፡ ”ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም” (1ኛ ዮሐንስ 2፥15-16)።
ክርስቲያን የሆነ ሰው ከላይ የተጠቀሰውን አይነት ሕይወት መኖር የሚችለው የመንፈስ ቅዱስን ምሪት ሲከተል ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ በቅድስና የተሞላ ሕይወት እንድንኖር ምሪትንና አቅምን ይሰጠናል፡፡ “እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል” (ዮሐንስ 16፥13)። የዚህ ሁሉ ውጤት የተለወጠ ልብና ከእምነት የመነጨ መታዘዝ የሞላበት ሕይወት እንዲኖረን ያደርጋል፡፡ እምነት ፍጹም የሚሆነው በስራ ነው (ያዕቆብ 2፥22)። እንዲህ ያለው ክርስቲያን ከዚህ በኋላ ለራሱ ከመኖር ይልቅ ለኢየሱስ ይኖራል፡፡
የመንፈስ ቅዱስ አብሮነት በክርስቲያን ልብ ውስጥ የጠለቀ ፍቅር እንዲሞላ ያደርጋል፡፡ እንደ እርሱ ዳግም የተወለዱ ክርስቲያኖች ሕብረትን የሚፈልግ ክርስቲያን ይሆናል፡፡ እንዲህ አይነት ህብረት እርስ በእርስ የልብን ሀሳብ መካፈልንና ግልጽ መሆንን የሚያበረታታና ለአንድ ክርስቲያን በመንፈሳዊ ሕይወቱ እንዲያድግ ድጋፍ የሚያገኝበት አንድነት ነው፡፡
ዳግም ስንወለድ ስማችን በሕይወት መጽሐፍ ይጻፋል፤ “በሕይወትም መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘው ማንኛውም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣለ” (ራእይ 20፥15)። ዳግም ስንወለድ ኃጢአታችን ይቅር ተብሎልን ደስታና ሰላምን በልባችን ማጣጣም እንጀምራለን፡፡ ሰይጣን ያገኘነውን ድነት ባለመታዘዝ ውስጥ ከቶ ሊያስጥለን ቢሞክርም እግዚአብሔር ግን ታማኝ ሆነን ከቆምን ከክፉ ሁሉ እንደሚጠብቀንና እንደሚያድነን ቃል ገብቶልናል፡፡ “እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም” (ሮሜ 8፥1)። “እግዚአብሔርን መምሰል የአሁንና የሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው፥ ለነገር ሁሉ ይጠቅማል” (1ኛ ጢሞቲዎስ 4፥8)።